ፍራሽ አዳሽ እንጂ
ፍራሽ ሰሪ ጠፍቶ
ነጭ አምላኪ ጥቁር
ነጭ ጠቃሽ በዝቶ
የሌላን አፍቃሪ
የራሱን አጥላልቶ
የሚሸምት ሰልባጅ
የፈረንጅ ድሪቶ
አንዴ “ማርክሲዝም”
አንዴ “ሌኒንዝም”
አንዴ “ሊብራሊዝም”
ሲመቸው “ሰርድ ዌይ”
ሲከፋው “ዲስትሮይ”
ባላገር ገርሞት ዝም
ብዙ እየሰማ ዝም
ዝምታው ሲገርም
ቁዝምዝም ቁዝምዝም
እያየ የተማሩ
ሲቀበዣዥሩ
አንዴ “ሪቮሉሽን”
አንዴ “ኢቮሉሽን”
አንዴ “ዲሞክራሲ”
አንዴ “ቢሮክራሲ”
ያሁን ደግሞ “ፋሽን”
“ዲኮንስትራክሽን”
“ትራንስፎርሜሽን”
ቀርቶ “ዳያሌክቲክ”
በርክቶ ንትርክ
ሳይቀር ሆድን ማከክ
ከዘመን ዘመናት
ከውጭ ሀገራት
የውጭ ፍልስፍና
ልክ እንደ ሳሙና
እየተሸመተ
አዕምሮ ሸበተ
በራስ ፍልስፍና
ዘንድሮ ካች አምና
ከራስ ተርፎ ለውጭ
ጥበብ የሚያመነጭ
ባይጠፋም ከሀገር
ሀገር የሚያስከብር
ሆኖም የለው ክብር
ገበሬ ባለ ቅኔ
አባ ገዳ ሸማኔ
ኮንሶ ባለ እርከን
አቶ አህመድ ሐሰን
እሥራኤል ቤሌማ
ያሬዳዊ ዜማ
እንዲሁም መንዙማ
ሀገር በቀል ምርጦች
ሀገር ሰራሽ ምርቶች
ትንሽ ነው ዋጋቸው
ለነጭ አድናቂ ሰው
ሩቅ ሩቁን የሚያይ
እንግሊዝ ፈረንሳይ
መቼ ሆኖ ነውር
ከሌሎች መማር
ከውጭ መገብየቱ
ነገር ግን ንውረቱ
የነጭ ሥራን መጥቀስ
ሲሆን ምሳ ራት ቁርስ
እሣት ለመለኮስ
ለማውደም ለማፍረስ
ነጭ በፈጠረው
በከንቱ መራቀቅ
የሀገሩን በሬ
ከቀምበር ሳያላቅ
በተዋሱት ነገር
ሲያቅት አዲስ መፍጠር
ፍሬያማ ምርምር
ያ ነው ትልቅ ነውር
በገበዩት እውቀት
ከራስ በላይ ማየት
ከራስ በላይ ማሰብ
ሁሉም እንዲያብብ
ሁሉም እንዲሰራ
ሁሉም እንዲኮራ
መፈላሰፍ ሲያቅት
ያ ነው ትልቅ ንውረት
የመማር ከንቱነት
ነጭ እየጠቀሱ
ተራ ፍልስፍና
ውጤቱ ኪሳራ
የእብደት ጎዳና
***
I guess I need to remind myself about my promise to learn Amharic.
those lovely dancing angels
haha you & amharic, mon amie
Very nice poem.
it belong with us………………
መልክቱን ወድጄዋለዉ